እምነትን የሰነቀ የከፍተኛ ትምህርት የደርሶ መልስ ጉዞና ስኬት

ዳዊት ቶሎሳ

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. 2011 የተቋቋመው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ አሜሪካ ካለው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ከድኅረ ምረቃ እስከ ቅድመ ምረቃ በጥራት ላይ የተመሠረተ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ ከምሥረታው ወዲህ ለ11 ጊዜ በኤምቢኤ እንዲሁም ለአምስተኛ ጊዜ በቢኤ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ ከዌስተር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር አቤቱ መላኩ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢትዮጵያ ትምህርት መስጠት እንዴት  ጀመረ?

አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በኦክላንድ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪዬን ለማጠቃለል የመጨረሻው ሴሚስተር በማገባደድ ላይ እያለሁ በአፍሪካ የነበረው ብቸኛው የሊንከን ኤክስቴንሽን በናይጄሪያ ሊዘጋ ነው የሚል መረጃ ሰማሁ። ከዚያም የዩኒቨርሲቲው ዋና የአካዴሚ ኦፊሰር ቢሮ በመሄድ እንዴት በአፍሪካ አንድ ተወካይ ዩኒቨርሲቲ ይዘጋል? በአፍሪካ አንድ ተወካይ ዩኒቨርሲቲ እንዴት አይኖርም? የሚል ጥያቄ አቀረብኩ።  ኦፊሰሩም በጊዜው በነበረው የደኅንነት ሥጋት መምህራን ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ  ሳይወጡ ሲያስተምሩ እንደነበርና ሥጋት ስላደረባቸው ለማቋረጥ እንደተገደዱ አብራሩልኝ። እኔም ለምን በኢትዮጵያ አይጀመርም የሚል ሐሳብ አቀረብኩ። እሳቸውም በኢትዮጵያ ስላለው የደኅንነት ሁኔታ ጠየቁኝ። እኔም ኢትዮጵያ ሰላም መሆኑን አስረድቼ፣ ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) አቅርቤና አስፈቅጄ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቅድሚያ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ኤክስቴንሽን የኤምቢኤ ፕሮግራም እንዲጀመር አደረግሁ፡፡ ቀጥሎም ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የሚሠራ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም በማቋቋም ሁለቱን ፕሮግራሞች አጣምረን  በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኮሌጁን የማቋቋምና ፈቃድ የማግኘት ሒደት ምን ይመስል ነበር?
አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡-  ትልመ ሐሳቡን ለሊንከን ዩኒቨርሲቲ አቅርቤ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እ.ኤ.አ. 2010 ላይ ኢትዮጵያ ያለውን ሒደት ጀመርኩ። በኢትዮጵያ ፈቃዱን ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩት። በጊዜው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማረጋገጫ አካል በኢትዮጵያ ትምህርት ለመጀመር ቀላል እንዳልሆነና ኮሌጁን ለመጀመር ሟሟላት ያለብኝን ነገር ዘረዘሩልኝ። አንደኛ ለአምስት ዓመት ለአስተማሪዎች የተከፈለ የደመወዝ መዝገብ (ፔሮል) እና የተቋሙን የቤት ኪራይ ውል ማቅረብ አለብህ የሚል ነበር። የተጠየቀውን መስፈርት ወዲያው ማምጣት ካልተቻለ፣ ፈቃዱን ማግኘት እንደማይቻል መልስ ተሰጠኝ። በሁኔታው በመገረም የተባለውን ውል በአንድ ጀምበር ከየት ነው የማመጣው የሚል ትዝብት የተሞላበት መልስ ሰጠሁ። ከዚም አንድ ጉዳዩ የገረማቸው ከፍተኛ የመንግሥት አካል ሰምተው እንዴት ይኼን የመሰለ በጥረት የተገኘ ዕድልና አጋጣሚ ይከለከላል ብለው ከሦስት ወር በኋላ ተመለስ ተብዬ፣ ተፈቀደ። ሲፈቀድ ግን ኮሌጁ ራሱን ችሎ ሳይሆን ፈቃድ ካለው የትምህርት ተቋም ጋር ተደርቦ ይሥራ በሚል ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን መቀጠል አልቻልንም። ምክንያቱም የእኛ የትምህርት ተቋምም ሆነ ፕሮግራም ጥራት በጣምራ እንድንሠራ  ከተደረገው ተቋም ጋር የሚነፃፀር  አይደለም የሚል ነበር።

ስለዚህ ለምን ራሳችሁን ችላችሁ አትሠሩም የሚል ሐሳብ በመቅረቡ፣ የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን መሥርተን ፈቃድ በማውጣት ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በየጊዜው በማዘመን ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ላይ እንገናኛለን።

ሪፖርተር፡- ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በተቋማችሁ የሚሰጠው የመማርና የማስተማር ሒደት ምን ይመስላል?

አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፊሰር )፡-  የማስተርስ የትምህርት ዝግጅት መርሐ ግብር ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰጥ ሲሆን፣ የባችለር ዲግሪ ፕሮግራም በዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በአገር ውስጥ መምህራን ይሰጣል። የሊንከን ዩኒቨርሲቲ መምህራንም የተለያዩ ኮርሶች በመስጠት ያግዙናል። ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስከገባበት ድረስ መምህራኑ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ፊትለፊት ትምህርቱን በክፍል ውስጥ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ለሚሰጠው የትምህርት ጥራት በማሰብ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 ተማሪ በላይ አናስተምርም። ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን። የእኛ ኮሌጅ የሚለየው የትምህርት ሥርዓቱ (ካሪኩለም)፣ መጽሐፉ፣ መምህራኑ እንዲሁም ዲግሪው 100 ዓመታትን ያስቆጠረው የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ነው።  ኮቪድ-19  እንደተከሰተ ካንቫስና ዙም የተባሉ የኦንላይን ሶፍትዌሮችን በመጠቀም  ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከሁሉም የትምህርት ተቋማት ቀድመን ተግባራዊ በማድረግ ትምህርቱን ለማስቀጠል በቅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎችን የሚለይበት መንገድ ምን ይመስላል?
አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡-  እኛ ተማሪ የምናስገባው ወረቀት አለኝ ስላለ አይደለም። ተማሪው ለመማር ያለውን ተነሳሽነትና ብቃት የምንለይበት መንገድ አለን። የቁጥጥር ዘዴው እጅግ የጠበቀ ነው። ተማሪ ክፍል ውስጥ መገኘት ግዴታው ነው። ፈተና ማለፍና ፕሮጀክት መሥራት ይኖርበታል። መምህሩ በአካል ተገኝቶ ነው የሚያስተምረው። እኛ የምንከተለውና የምንተገብረው የድሮውን የመማርና ማስተማር ሒደት ነው።  የአገር ውስጥ መምህራንን በጥንቃቄ በመምረጥ የተሻለ ክፍያ እንዲከፈላቸው እናደርጋለን፡፡ መቅረት አይፈቀድም። እኛ ለብለብ አድርጎ መልቀቅ አይቻልም።

ሪፖርተር፡- ኮሌጁ የመክፈል አቅም ላላቸው ጥቂት ተማሪዎች ብቻ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ይነገራል። አሁን ካለበት በማስፋት የመቀበል አቅሙን አሳድጎ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሌሎቹም ተጠቃሚ ማድረግ ለምን አልተቻለም?

አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ተቋማችን በአሁኑ ወቅት ከግለሰብ ቤት ተከራይቶ ነው ተማሪዎች እያስተማረ የሚገኘው። ተቋሙን ለማስፋት፣ ሁሉንም የትምህርት ግብዓት መስጠት እንዲቻል የራሱ የሆነ  ካምፓስ እንዲኖረው ማድረግ አስበናል፡፡ የፕሮጀክቱን የተሟላ ጥናት አጥንተን፣ የፋይናንስ ድጋፍና የረጅም ጊዜ ብድር ለማግኘት ቀደም ሲል ኦቨርሲስ ፕራይቬት ኢንስቨስትመንት ኮርፖሬሽን፣ አሁን ደግሞ ዴቨለፕመንት ፋይናንሻል ኮሮፕሬሽን  ለሚባለው የፋይናንስ ተቋም አመልክተናል፡፡ እኛም ልንገነባው ያሰብነውን የካምፓሱን ፕሮጀክት ንድፍ ካቀረብን በኋላ፣ ማሻሻል ያለብንን ነገር አሻሽለን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰን ነበር። ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ባደረገው የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ለጊዜው ብድሩን ያዝ አድርገውታል። ፕሮጀክቱ በሒደት እስከ አምስት ሺሕ ተማሪ የመያዝ አቅም ሲኖረው ትምህርቱንም በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚያስችል ነው። እንደሚታወቀው ትምህርት ቤታችን ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ክፍያ ይጠይቃል። ግን የእኛ ትምህርት ቤት ለመክፈል አቅም ያላቸውን ለማስተማር  የተቋቋመ አይደለም። በዚህም መሠረት ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጥሩ ውጤት ያላቸውና ቤተሰቦቻቸው የመክፈል አቅም የሌላቸውን በተለይ ሴት ተማሪዎችን አወዳድረን ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ማኅበራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ጥረት ይደረጋል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በ2013 ካስመረቅናቸው ተማሪዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ኮከብ ተሸላሚ የሆነችው ጁሀራ ሁሴን ተቋማችን የትምህርት ዕድል ሰጥቶ ያስተማራት ብሩህ ወጣት ናት፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ መንግሥት የተያዘውን ፋይናንስ ለማስለቀቅ ሟሟላት አለባችሁ ተብሎ የተቀመጥ መመዘኛዎች ወይም መስፈርቶች ምንድናቸው?

አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ይኼ ብድርና ዕርዳታ እንዲለቀቅ በቀዳሚነት የተጠየቅነው ጉዳይ፣ የከተማ አስተዳደሩ ለግንባታው የሚያስፈልገውን መሬት በተመጣጣኝ ዋጋ መስጠት አለበት የሚለው ነው፡፡  መሬቱ የማይሰጥ ከሆነ ብድሩም አይለቀቅም ብለውናል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን እንዲፈቅድ ፈብዳቤ አስገብተናል።  ጥናቱም ሆነ የቦታ ጥያቄው የቀረበው በወቅቱ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ለነበሩት አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ዘመን ነው፡፡ ጥያቄያችን ወደ መሬት አስተዳደር ቢላክም ቦታው ላይ የነበሩት አመራሮች ወዲያው ወዲያው መቀያየራቸውን ተከትሎ፣ ሊሳካ አልቻለም። የአሁኗ የከተማዋ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተመልክተው ተገቢውን መመርያ እንዲሰጡልን ለማድረግ ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በመሬት አስተዳደሩ በየጊዜው የተሄደበትን መንገድና የተጻፉትን ደብዳቤዎችና የሄድንበትን ውጣ ውረድ በማስረጃ በማስደገፍ ለጽሕፈት ቤት ኃላፊው ደብዳቤ ብናስገባም፣ እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ክስተቶች ምክንያት እየተደረጉ፣ ጉዳዩ ተንከባሎ እዚህ ደርሷል።  በአንድ ወቅት የመሬት አስተዳደሩ ለከተማ ልማትና እድሳት ክፍል ተጣርቶ መሬቱ ይሰጣቸው ተብሎ ቢመራም፣ እስካሁን አላገኘንም። ጉዳዩን ውስብስብ በማድረግ መቋጫ እንዳያገኝ ያደረገው በከተማው የመሬት አስተዳደር ኃላፊዎች በየጊዜው መቀያየር ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዕውቅና ማረጋገጫ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ኮሌጁ ፍቃድ የለውም ተብሎ ሲነሳ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስለ ጉዳዩ ቢያብራሩልን?

አቤቱ (ተባባሪ ፕሮፊሰር)፡- የብቃት ማረጋገጫ ፍቃዱ የሚታደሰው በየአምስት ዓመት ነው፡፡ ከአሁን በፊት ለሁለቴ የታደሰልን ቢሆንም፣ ለሦስተኛ ጊዜ ለማደስ 2012 ዓ.ም. ላይ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አሟልተንና ክፍያ ፈጽመን አመልክተናል፡፡ ኮቪድ-19 እና ሌሎች ምክንያቶች እየተሰጡ ለስምንት ወራት ካዘገዩ በኋላ ያለ አግባብ፣ ሆነ ብለው ‹‹የብቃት ማረጋገጫ  ፈቃድ የላቸውም›› ብለው የትምህርት ቤታችንን ስም ያለ አግባብ በማጠልሸት ደብዳቤ ተጽፏል፡፡ መግለጫው በተሰጠበት ወቅት በተማሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ የፈጠረው አለመረጋጋትና መረበሽ ቀላል አልነበረም፡፡ ይህ የማይታመን ጉዳይ ሲፈጸም በእኛ በኩል የወሰድነው አቋም ሰው በአገሩና በወገኑ እንዴት ተስፋ ይቆርጣል? እስከ መቼስ ይጨልማል በማለት፣ የያዝነውን የቀደመ መርህ መሠረት በማድረግ፣ በጨለማ ጊዜ የገነባነውን ተቋም በብርሃን እንዳይፈርስ ለማድረግ ሸብረክ ሳንል በጽናት በመቆምና በመመከት ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ ለሚመለከተው የበላይ አካላት በማሳወቅ በጽናት ታግለናል፡፡ እውነታው በእኛ በኩል ያለ መሆኑን ስለምንገነዘብ በበለጠ ተጠናክረን እንደምንወጣ አንጠራጠርም፡፡

Source:- https://ethiopianreporter.com/article/24066