ዳዊት ቶሎሳ
በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮችና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሰማሩት የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጣቸው፡፡ ይህንን የክብር ዶክትሬት የሰጣቸው አሜሪካ አገር 100ኛ ዓመቱን በዚህ ዓመት ካከበረውና አዲስ አበባ ቅርንጫፉ የሆነው የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የ2020 የኮሌጁ ተማሪዎች የምረቃ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
የክብር ዶክትሬት የተሰጠበት ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ከሥራ ፈጣሪነት፣ ምንም ገቢ ከሌለው ችግረኛ ቤተሰብ ተፈጥሮ ብዙ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራ በመሥራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚለው አንዱ ነው፡፡ አነስተኛ የገቢ መጠን ያላቸው ቤተሰብ ልጆችና የትምህርት ዕድል ላጡ ታዳጊ ወጣቶች የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በመሥራት ላለፉት አሠርታት 1,300 በላይ ተማሪዎች ድጋፍ የሚያደርግ ፋውንዴሽን ሙሉ ወጪውን በመቻል፣ እየደገፉና አሁንም ይህንኑ ተግባራቸውን የቀጠሉ በመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በቅርቡም ግንባታው የሚጠናቀቀውና ለአምስት መቶ የሚሆኑ የአረጋውያን መጠለያ ሙሉ ወጪውን በመቻል የማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ባላቸው ቁርጠኛ ፍላጎት ምክንያት የክብር ዶክትሬቱ እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሠራተኛ ጋር ያላቸው ግንኙነትም በመልካም የሚታይና የጠበቀ በመሆኑና በየአምስት ዓመት ከሃያ ለሚበልጡ ሠራተኞች ቤት በመሸለም እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ታሳቢ ተደርጎ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣቸው መሆኑን የክብር ዶክትሬቱ የተሰጠበትን ምክንያት የሚያሳየው መረጃ ያመለክታል፡፡
የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም አቶ ሳሙኤል እርሳቸውና ሰንሻይን የተሰኘው ኩባንያቸው ከትናንት እስከዛሬ የተጓዙበትን መንገድና የሕይወት ትረካቸውን የሚያስቃኝ ተግባር የሚል መጠሪያ የተሰጠው በአማርኛና በእንግሊዝኛ የታተመ መጽሐፋቸውም ይፋ ሆኗል፡፡
‹‹ተግባር የተሰኘው መጽሐፌ እኔና ሰንሻይን ከትናንት እስከዛሬ በሕይወት ዘመኔ የደረስኩበትንና የሆኑኩትን በአጭሩ የሚያወጋ ብቻ ሳይሆን የተፈተንኩባቸውን አጋጣሚዎች በምን አኳኋን እንደተወጣኋቸው የሥራ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ተሞክሮዎቼን በተለይም ደግሞ ለመጪው ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ የራሴን አሻራ ለመተውና የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት በማሰብ ያዘጋጀሁት ነው፤›› በማለት ስለመጽሐፉ ገልጸዋል፡፡
የክብር ዶክትሬት ማግኘታቸውን አስመልክቶ እንደገለጹትም፣ ‹‹የክብር ዶክትሬት ስቀበል ከዛሬ 35 ዓመታት በፊት የነበርኩበትን ቦታ እንዳስታውስና በወቅቱ ከምንም ተነስቼ ያገኘሁትን ሥራ አክብሮ በመሥራት በአሁን ወቅት በሥራ ፈጣሪነት ብዙ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ሰፊ ኢንቨስትመንት በማቋቋም ከስድስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡›› ከሁሉ በላይ መንፈስን በደስታ በሚሞላ በጎ አድራጎት ሥራ ላይ በመሳተፍ አነስተኛ የገቢ መጠን ያላቸውን ቤተሰብ ልጆች እንዲሁም የትምህርት ዕድል ላላገኙ ታዳጊ ወጣቶች የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በመገንባት መማር ማስቻላቸው ነው፡፡ መማር እየፈለጉ ላልቻሉ ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ዜጎችን ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብ በጎ አድራጎት በመክፈት የትምህርት ቤቶች የገነቡት በኦሮሚያ ክልል ነቀምት፣ በትግራይ ክልል አክሱም፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል አገና ነው፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ላለፉት ሦስት አሠርታት በሦስቱም ክልሎች በአጠቃላይ ከ1,300 በላይ ተማሪዎችን 200 ብር የኪስ ገንዘብ ጨምሮ አጠቃላይ ወጪው በየወሩ 850 ሺሕ ብር በማውጣት ድጋፍ እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ እየተሠራ ያለው ትምህርት ቤት በ2013 ዓ.ም. የሚከፈት ሲሆን፣ ተጨማሪ 300 ተማሪዎችን በመጨመር በአጠቃላይ 1,600 ተማሪዎችን እንደሚያስተምር አመልክተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ራሱን ማስተዳደር የሚችል ዘመናዊ የሆነ የአረጋውያን መንደር በመገንባት 250 ክርስቲያንና 250 እስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑ በአጠቃላይ 500 ለሚሆኑ አረጋውያን መጠለያ በ65 ሚሊዮን ብር ወጪ በመመደብ ግንባታው ተጠናቆ በ2013 ዓ.ም. ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ሳሙኤል ከበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸው ባሻገር በኢንቨስትመንት መስኩ ስላበረከቷቸው ተግባራት የሚገልጸው መረጃ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ወደ 16 የሚሆኑ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን ማከናወናቸው ይጠቀሳል፡፡ በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይም በተመሳሳይ ሰፋፊ ሥራዎች ስለመሥራታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡም በሆቴል ኢንቨስትመንት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የማሪዎት ኤክስኪውቲቭ አፓርትመንት ግንባታን በማጠናቀቅ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ሁለተኛውን የማሪዮት ሆቴል በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሆቴል በ2014 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ በሐዋሳ ከሒልተን ዓለም አቀፍ ጋር በመሆን የሐዋሳ ሒልተን ሪዞርት ግንባታም በመካሄድ ላይ እንደሆኑ በተግባር መጽሐፋቸው ላይ ተገልጿል፡፡ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር የሚሠራ ነው፡፡
እንደ አቶ ሳሙኤል ሁሉ ከዚህ ቀደም ለኢስት አፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ለአቶ ብዙአየሁ ታደለ በተመሳሳይ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ 81 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
Source:- https://ethiopianreporter.com/index.php/article/17998